በረከት ብርሃኑ ሞሲሳ፣ ዮናስ ካሳ በጋሻው እና ዳግም ውብሸት ወንድማገኝ የተባሉት ተከሳሾች÷ በሌላ ችሎት አቅርበውት የነበረው ሕዝባዊና መንግሥታዊ የቅጣት ማቅለያ ሠነዶች ሐሰተኛ መሆናቸውን በማጣራት የሙስና ወንጀልን ለመከላከል በወጣው ዐዋጅ ሥር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸው ነበር።
ከሁለት ዓመት በፊት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በከባድ ውንብድና ተግባር በተከሰሱበት የወንጀል ተግባር የግራ ቀኝ ማስረጃ ተጣርቶ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ባለመከላከላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል፡፡
ይሁንና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 82 እና አንቀጽ 86 መሠረት የሚጣልባቸው ቅጣት እንዲቀልላቸው ለቅጣት ማቅለያነት የሚውሉ ሐሰተኛ መንግሥታዊና ሕዝባዊ የሠነድ ማስረጃዎችን ማቅረባቸው ተጠቅሷል፡፡
1ኛ ተከሳሽ ከሁለት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጉን፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ደም መለገሱን፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 የማኅበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ እና ለአረንጓዴ ዐሻራ ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ መግዛቱን የሚገልጹ ሐሰተኛ የሠነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል ተብሏል፡፡
2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችም በየደረጃው ሕዝባዊና መንግሥታዊ የሆኑ ለቅጣት ማቅለያነት የሚያገለግሉ ሐሰተኛ ሠነዶችን በማቅረብ ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ቅጣቱ ቀልሎ እንዲወሰን ያደረጉ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ ክስ አቅርቧል፡፡
የቀረበውን ሐሰተኛ የቅጣት ማቅለያ ማስረጃ ሠነዶችን ማቅረብ ክስና የግራ ቀኝ ክርክር የመረመረው 2ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ወንጀሉን መፈጸማቸውን በማረጋገጥ ጥፋተኛ ብሏዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም÷ 2ኛ ተከሳሽ በ2 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራትና በ500 መቶ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡
በታሪክ አዱኛ