በቬትናም ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት ፑቲን÷ ምዕራባውያን ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጣለባትን ማዕቀብ በመቃወም የኒውክሌር እና የባላስቲክ ሚሳኤሎችን ሰርታለች በሚል ያገለሏት ሀገር እንደሆነች ጠቅሰዋል።
ምዕራባውያኑ በሞስኮ እና በፒዮንግያንግ መካከል እያደገ የመጣውን ግንኙነት አሳሳቢ አድርገው ይመለከቱታል ብለዋል።
ፑቲን ሩሲያ ከምዕራባውያን ጋር መልካም ግንኙነት ለሌላቸው ሀገሮች የጦር መሳሪያ ልታቀርብ ትችላለች ሲሉ መዛታቸውም ይታወሳል፡፡
ለዚህ ምክንያቱም ምዕራባውያን ለዩክሬን ከፍተኛ የጦር መሳሪያ እያቀረቡ እና በሩሲያ ውስጥ ባሉ ኢላማዎች ላይም እንዲተኮስ ፍቃድ እየሰጡ እንደሆነ አመላክተዋል።
በቅርቡ በሰጡት አስተያየትም ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ የጦር መሳሪያ ከሚቀበሉ ሀገራት አንዷ ልትሆን ትችላለች ብለዋል።
ከሰሜን ኮሪያ ጋር የተገቡትን ስምምነቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ፒዮንግያንግን ጨምሮ ለተለያዩ የዓለም ሀገራት የጦር መሳሪያ የማቅረብ መብታችንን እናስከብራለንም ነው ያሉት፡፡
ከትናንት በስቲያ በሩሲያና ሰሜን ኮሪያ መካከል የተፈረመው ስምምነት እያንዳንዱ ወገን በአንደኛው ላይ የትጥቅ ጥቃት ሲደርስ አፋጣኝ ወታደራዊ እርዳታ እንዲሰጥ የሚያስገድድ መሆኑን ኢንዲያ ቱዴይ ዘግቧል።
ነገር ግን ከዩክሬን ጋር ለገቡበት ጦርነት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማያስፈልጋቸውና እስካሁንም ድጋፍ ያደረገላቸው አካል አለመኖሩን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ አሜሪካና ዩክሬን ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የመድፍ ተተኳሾች እና ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አቅርባለች ይላሉ።