የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ አፍሪካ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ትምህርት

By Feven Bishaw

June 21, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ አፍሪካ በታሪኳ ሁለት የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን አስተናግዳለች፡፡

ኮዴሳ (Convention for a Democratic South Africa – CODESA) በመባል የሚታወቀውና እና እ.አ.አ ከ1991 እስከ 1993 የተካሄደው የምክክር ሂደት የመጀመሪያው የሀገሪቱ የምክክር እርምጃ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የሂደቱ ዋነኛ ዓላማ በወቅቱ የነበረውን ስርዓት ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማስወገድ ከዘር መድልዎ ነፃ የሆነች ሀገርን መፍጠር ነበር፡፡

በተጨማሪም ሀገሪቱ በጊዜያዊነት የምትተዳደርበትን ሕገ-መንግስት የማዘጋጀትን ዓላማም አንግቦ የነበረ ሲሆን÷ በሂደቱ እጅግ ብዙ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮች በንግግር እንዲፈቱ በር ከፋች መሆን መቻሉ ይገለፃል፡፡

ሁለተኛውና በሀገሪቱ የተተገበረው የምክክር ሂደት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊዎች የነበሩበት የድርድር መድረክ Multiparty Negotiation Process – MPNP በመባል የሚታወቀው ነው፡፡

ሂደቱ በፈረንጆቹ 1993 የተካሄደ ሲሆን÷ ቀደም ሲል ተካሂዶ የነበረውን የምክክር ሂደት መሰረት አድርጎ የተነሳ ነበር፤ ይህ ሂደት እጅግ አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት ሲሆን የሀገሪቱ ሀይሎች የተስማሙበትን ጊዜያዊ ሕገ-መንግስት በጋራ ማፅደቃቸው ነው የሚወሳው፡፡

ታዲያ ኢትዮጵያ ከዚህ ምን ልትማር ትችላለች? 👉 አካታችነት እና አሳታፊነት በደቡብ አፍሪካ በተደረጉት ሁለቱም የሀገራዊ ምክክር ምዕራፎች የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና የሀሳብ ውክልና በእጅጉ የደረጀ ነበር፡፡ ያ በመሆኑም ሀገሪቱ መግባባትን ለመፍጠር የምትችልበትን ቁመና በአጭር ጊዜ ለማምጣት አስችሏታል፡፡ 👉 ስምምነት ላይ ለመድረስ መስዋዕትነትን መክፈል በሀገሪቱ በተደረጉት ሁለቱም ሂደቶች ያለፉ የፖለቲካ ሀይሎች መግባባትን ዋነኛ ዓላማቸው አድርገው ወደ ሂደቱ በመግባታቸው ሁሉም በየበኩላቸው እጅግ ከባድ ሊባሉ የሚችሉ የመርህ እና የአቋም ማስተካከያዎችን አድርገዋል፡፡ ይህም ሂደቱን ስኬታማ ከማድረጉም በላይ ሌሎች ሀገራት ከሂደቱ ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ትምህርት አስቀምጦ አልፏል፡፡

ለምሳሌ በሂደቱ ተሳታፊዎች በነበሩ አንዳንድ ባለድርሻ አካላት በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ጥቁሮች ያጡትን የመሬት ባለቤትነት ለማስመለስ እጅግ ጠንካራ አቋም ነበራቸው፡፡ ሆኖም ግን በምክክሩ ሂደት ይህ አቋማቸው ላይ ማስተካከያዎችን በማድረግ በነጮች የተያዙ ይዞታዎች ሳይነኩ ለወደፊቱ ግን የመሬት አዋጅ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

👉 በተለያዩ ዙሮች እና ምዕራፎች መካሄዱ

ከላይ እንደተገለፀው የደቡብ አፍሪካ የሀገራዊ ምክክር ሂደት በሁለት ተከታታይ ዙሮች መካሄዱ በሂደቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላት ሚዛናዊ ውሳኔዎችን እና አካሄዶችን እንዲከተሉ በር ከፋች ነበር፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ጊዜ ለሂደቱ መሳካት ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን ሲሆን ባለድርሻ አካላትም በጊዜ ሂደት ነገሮችን በጥልቀት እና በሰከነ መንፈስ ለማየት ዕድሉን ያገኛሉ፡፡

👉 ትዕግስት እና ፅናት

ደቡብ አፍሪካውያን ለዘመናት በቆየው የአፓርታይድ አገዛዝ እና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች የውስጥ ሰላማቸውን አጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን በሀገሪቱ የምክክር ሂደቶች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ተዋናዮች ለሂደቱ መሳካት ያሳዩት ትዕግስት እና ፅናት ሂደቱን ውጤታማና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን አድርጎታል፡፡

መረጃው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው