አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሁለተኛው ዙር የምድብ ማጣሪያ መርሐ ግብር ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
በዚህ መሰረትም በምድብ አራት የሚገኙት ፈረንሳይ እና ኔዘርላድስ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
በመጀመሪያው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ፈረንሳይ ኦስትሪያን 1 ለ 0 እንዲሁም ኔዘርላንድስ ፖላንድን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
እኩል 3 ነጥብ ያላቸው ፈረንሳይ እና ኔዘርላድስ ከምድቡ በቀዳሚነት ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተመሳሳይ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ከዚሁ ምድብ በመጀመሪያው የምድብ ማጣሪያ ሽንፈትን ያስተናገዱት ፖላንድ እና ኦስትሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በተጨማሪም ቀን 10 ሰዓት ላይ ስሎቫኪያ እና ዩክሬን ሁለተኛው ዙር የምድብ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
በመጀመሪያው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ስሎቫኪያ ቤልጂየምን 1 ለ 0 ያሸነፈች ሲሆን÷ ዩክሬን ደግሞ በሮማንያ 3 ለ 0 መሸነፏ ይታወሳል፡፡