አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያሉንን የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ልማት በመቀየር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በሀዲያ ዞን ጊቤ ወረዳ የሀንዶሼ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክ መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡
አቶ እንዳሻው በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ የሀዲያ ዞን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ነው ብለዋል።
ያሉንን የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ልማት በመቀየር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በትኩረት ይሰራልም ሲሉ ተናግረዋል።
ክልሉ ከተመሰረተ የ10 ወራት እድሜ እንዳስቆጠረ በመግለጽ ህዝቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በጊቤ ወረዳ እየለማ ያለው ጥብቅ ደን ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከሚኖረው የላቀ ፋይዳ አንጻር ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
አመራሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል።
በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ፣ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ፣ የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ኑሪዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ በክልሉ በተያዘው የምርት ዘመን አዲስ የተጀመሩ የመስኖ ግንባታዎችን ጨምሮ 3ሺህ 128 ሄ/ር መሬት በመስኖ እየለማ ነው፡፡
በዚህም ከ12 ሺህ 800 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 15 የመስኖ ተቋማት በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖ እና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በበኩላቸው ፥ የሀንዶሼ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክ ከ26 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ብር ወጪ ተደርጎበታል።
ከ65 ሄ/ር በላይ መሬት የሚያለማ መሆኑን ተናግረውም ፥ 300 አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።