Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከጽንፈኛ ቡድን ጋር ተያይዞ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጽንፈኛ ቡድን ጋር ተያይዞ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የህገ-መንግስትና በህገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚጸሙ ጉዳዮችን የሚመለከተው ወንጀል ችሎት ዛሬ በሁለት መዝገብ የተከፈሉ የ11 ተጠርጣሪዎች ላይ የተመሰረተውን የሽብር ወንጀል ክስ ዝርዝርን ተመልክቷል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በአንደኛው መዝገብ ቴድሮስ ኃ/ማርያም ገድሉ (ዶ/ር)፣ ብርሃኑ ስነሺ ከበደ፣ እስክንድር ሺፈራሁ ትርፌ፣ ህይወት አለማየሁ ዲንቁ እና አሮን ተረፈ ወ/መድህን የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ተግባር መፈጸም ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾቹ የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግስትን በኃይል ለማውረድ በማሰብ እራሱን የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎና የሸዋ ፋኖ በማለት በቡድን ከተደራጀውና የጦር መሳሪያ ይዞ ጦርነት የከፈተውን ጽንፈኛ ቡድን በገንዘብና በጦር መሳሪያ በመደገፍ፣ በሌላ መዝገብ ከተከሰሱ ግለሰቦች ጋር ከአማራ ክልል እስከ አዲስ አበባ የሚል ስትራቴጂካዊ ሰነድ መቅረጽ፣ የፖለቲካ አመራርነት መስጠት፣ የጽንፈኛ ኃይሉ በመንግስት ላይ ጥቃት እንዲከፍት ማነሳሳት፣ በአማራ ክልል በተለያዩ ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማነሳሳትና ጥቃት በማድረስ ተግባር መሳተፍ፣ ጽንፈኛ ቡድኑን የሚደግፉ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች ገንዘብ ተቀብሎ ለጽንፈኛ ኃይል ማከፋፈል፣ በክልሉ የሚገኙ የሚሊሻ ጽ/ቤቶችን፣ ማሰልጠኛዎችን ባንኮችና የተለያዩ ተቋማትን ገንዘብና ንብረት ማዘረፍና መዝረፍ፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ላይ በንጹሃንና በፀጥታ አካላት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረግ የሚሉ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።

በሌላኛው ሁለተኛ መዝገብ ደግሞ ሙሉጌታ አይተንፍሱ፣ መራዊ አማረ፣ ይረድ ገዳሙ እና ቸርነት ዘመነን ጨምሮ 6 ግለሰቦች ደግሞ የሀገሪቱን ሰላምና ህልውና መጠበቅ ሲገባቸው ከፋኖ ጽንፈኛ ቡድን ጋር ሚስጢራዊ ግንኙነት በማድረግ፣ ጦር መሳሪያና መረጃ በማቀበል በመደገፍ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመከላከያ ሰራዊትን መልካም ስምና ክብር የሚያጎድፉ መልክቶችን እና ግጭት ቀስቃሽ መልክቶችን በማስተላለፍ፣ በአ/አበባ ኮዬፌጬ አካባቢ ኪዳነምህረት የሚል ማህበር በማደራጀትና አባላትን በመመልመል፣ ለጽንፈኛ ቡድኑ የሚውል ተቀጣጣይ ፈንጂ መስሪያ የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብ ጽንፈኛ ቡድኑን መደገፍ የሚል ተደራራቢ ክስ የተሳትፎ ደረጃቸው ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ ቀርቦባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎችን ማንነት በማረጋገጥ፣ ክሱ እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ የክሱን ዝርዝር በንባብ አሰምቷል።

ተከሳሾች በአዋሽ አርባ በነበረ የእስር ጊዜያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል በማለት አቤቱታ በቃል ያቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በጽሁፍ እንዲያቀርቡ በማለት በሁለቱም መዝገብ የዋስትና ክርክርና የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ በየመዝገባቸው ለሰኔ 26 እና 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version