Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀም የሚባክነውን ሃብት ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር የሙከራ ትግበራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀም የሚባክነውን ሃብት ለመቆጣጠር የሚያስችል የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት በ13 የመንግስት ተቋማት የሙከራ ትግበራ ተጀመረ።

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት የሙከራ ትግበራ ከሚደረግባቸው 13 የፌዴራል መንግስት ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል።

ኢ-ፍሊት ማኔጅመንት ማለት ክንውኖችን በጥራት፣ በብቃት፣ በሰዓት እና በበጀት መጥኖ መፈፀም የሚያስችል ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ነው።

በተለይም የተሽከርካሪ ንብረት አጠቃቀም፣ አያያዝ፣ የግዥ ሂደትና አወጋገድን በተመለከተ የላቀ ጠቀሜታ ያለው የአሰራርና ቁጥጥር ስርዓት መሆኑ ይነገራል።

በመሆኑም የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀም የሚባክነውን ሃብት ለመቆጣጠር በ13 የመንግስት ተቋማት የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት የሙከራ ትግበራ ጀምሯል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ÷ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የለማው የኢ-ፍሊት ማኔጅመት መተግበሪያ የተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀምን ከማሻሻል ባለፈ የሃብት ብክነትን የሚያስቀር መሆኑን ጠቁመዋል።

መተግበሪያው ተሸከርካሪ ያለበትን ቦታ የማመላከት፣ ከተሽከርካሪ ጥገና እና ነዳጅ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን መከታተል የሚያስችል መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሙከራ ትግበራ ከሚደረግባቸው ተቋማት መካከል የገንዘብ ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴር የሚጠቀሱ ሲሆን የየዘርፉ ሃላፊዎች የዲጅታል አሰራሩ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ሊፈታ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

Exit mobile version