አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሁለት ሀገር በቀል የፋርማሲዩቲካል አምራች ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተፈራርሟል።
የውል ስምምነቱን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና የሁለቱ ኩባንያዎች ባለቤቶች ተፈራርመዋል።
አቶ አክሊሉ ታደሰ በስምምነቱ ወቅት÷ ኮርፖሬሽኑ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በሰጠው ትኩረት በፓርኮች ውስጥ ያሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከነበረበት 10 በመቶ ወደ 55 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
“መሬታችን ለባለሃብቶቻችን” በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
በዛሬው እለት የውል ስምምነት የተፈራረሙት ሁለት ኩባንያዎች በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የለማ መሬት በመውሰድና የራሳቸውን ማምረቻ በመገንባት የሜዲካል ግሎቭ፣ ዊልቼሮችን፣ ስትሬቸሮችን እና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን የሚያመርቱ ይሆናል ተብሏል፡፡
ኩባንያዎቹ ከ200 በላይ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል መባሉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡