የሀገር ውስጥ ዜና

የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ባንኩ በዘርፉ ከሚኖሩ ለውጦች ጋር እንዲጣጣምና የቁጥጥር አቅሙን እንዲያጎለብት ያስችለዋል ተባለ

By Shambel Mihret

June 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ባንኩ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ከሚኖሩ ለውጦች ጋር እንዲጣጣም እና የቁጥጥር አቅሙን እንዲያጎለብት እንደሚያስችለው ተገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ጉባዔ÷የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ ማሻሻያ ሳይደረግበት ለ16 ዓመታት እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን÷ሰፋ ያሉ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ክፍተቶች እንዳሉበት መታየቱ በጉባዔው ተነስቷል፡፡

በመሆኑም በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ከሚኖሩ ለውጦች ጋር በሚጣጣም መልኩ የብሔራዊ ባንክን ስልጣንና ተግባር እንደገና በመወሰን የቁጥጥር አቅሙን ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የብሔራዊ ባንክ አደረጃጀት፣ አላማና ተግባር፣ ስለ ብሔራዊ ባንክ አስተዳደር፣ ባንኩ ከመንግስትና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነትና ሌሎችንም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች አካትቶ ይዟል ተብሏል፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና ማስተዳደሪያ ረቂቅ አዋጅን ላይ ከተወያየ በኋላ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ÷ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ የተጎሳቆሉ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግና የደን ልማትን በማስፋፋት የሚለቀቀውን የካርበን ጋዝ ልቀት ለመቀነስ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ለአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ቋሚና ተቋማዊ ስርዓት ያለው የፋይናንስ ስርዓት እንዲኖር ማስቻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የምክር ቤት አባላት÷የሚተከሉ ችግኞች ጸድቀው በረሃማነትን ለመከላከልና ምርታመነትን ለመጨመር በሚያስችል ሁኔታ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

በዘላቂነት እየለሙ ያሉ ተፋሰሶችን በእውቀትና በቴክኖሎጂ አቀናጅቶ መምራት እንደሚያስፈልግም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡

በዚህም የሥራ እድል ፈጠራ ጥያቄን እንዲመልሱ አቀናጅቶ አመራር መስጠት እንደሚያስፈልግ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

በተጨማሪም ጉባዔው የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ እና የፌዴራል የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በየሻምበል ምህረት