የሀገር ውስጥ ዜና

በቀጣዮቹ 10 ቀናት በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የዝናቡ ስርጭት ተጠናክሮ ይቀጥላል

By Melaku Gedif

June 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ አስር ቀናት በሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የዝናቡ ስርጭትተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በቀጣዮቹ 10 ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና በመካከለኛው የሀገሪቱ ሥፍራዎች ላይ ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ የሚጠናከሩበትና የሚስፋፉበት ጊዜ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከቀን ወደ ቀን በተሻለ መልኩ እንደሚጠናከሩ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የዝናቡ ስርጭት በመጠንም ይሁን በስርጭት የሚስፋፋበት ጊዜ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖር ተጠቅሷል፡፡

በመሆኑም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በመካከለኛው እና በሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በቀጣዮቹ 10 ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ፣ ኢሉባቦር፣ ጅማ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፣ ሰሜን ሸዋ(ሰላሌ)፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፤ ከአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፣ አዊ፤ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋና ዋህግምራ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ከትግራይ ክልል ማዕከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ፤ ምስራቅና ደቡብ ዞኖች፤ አዲስ አበባ፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ ፓዌ፤ አሶሳ እና ካማሺ ዞኖች፤ ከጋምቤላ ክልል ማዣንግ እና አኝዋክ ዞኖች፤ ከሱማሌ ክልል ሲቲ እና ፋፋን ዞኖች፤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ፣ ሀላባ፣ ስልጤ፣ ጠምባሮ፣ ሃዲያ፣ የየም ልዩ ዞን፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ፣ ጋሞ፣ ኮንሶ፣ ወላይታ፣ ጌድኦ፣ አማሮ፣ አሪ እና ደራሼ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ ሀረር እና ድሬዳዋ ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለወ ዝናብ የሚያገኙ ይሆናል፡

በተጨማሪም ከዕለት ወደ ዕለት ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ገጽታዎች ላይ በመነሳ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ፣ ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች፤ ከሶማሌ ክልል ጀራር፣ ኤረር፣ ኖጎብ፣ አፍዴር፣ ሊበን እና ዳዋ ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ቅልበቲ፣ ፈንቲ፣ አውሲ እና ሀሪ ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን፤ ከጋምቤላ ክልል ንዌር እና የኢታንግ ልዩ ዞን ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡