አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያዊቷ መቅደስ ከበደ ከወገቧ ታጥፋ (ማርኔሊ ቤንድ) ተሸከርካሪ ቁስን በጥርሷ ነክሳ በመያዝ ለአንድ ደቂቃ በመሽከርከር ያሳየችው ትርዒት የዓለም ክብረ ወሰን በመሆን በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ መዝገብ ሰፈረ፡፡
ማሪኒሊ ቤንድ ጭንቅላታቸውን ከስር በማድረግና መሬት ላይ ያረፈን ተሸከርካሪ ቁስን በጥርስ ነክሶ በመያዝ ከወገብ በመታጠፍ የሚሰራ የሰርከስ ትርዒት ሲሆን፥ ይህም የሰውነታቸውን ክብደት በሙሉ ጥርስ እንዲሸከም ያደርጋል፡፡
የሰርከስ ትርዒቱ እጅግ በጣም አደገኛ እና ከባድ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
በዚህ የሰርከስ ዓይነት ነው እንግዲህ ኢትዮጵያዊቷ መቅደስ ከበደ ለአንድ ደቂቃ በመሽከርከር ያሳየችው ትርዒት የዓለም ክብረወስን በመሆን በትናንትናው ዕለት በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ መዝገብ ላይ ስሟ የሰፈረው።
መቅደስ ከበደ ትርዒቱን ያሳየችው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ በጣሊያን ሚላን መሆኑ ይታወቃል።