የሀገር ውስጥ ዜና

በመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ሲመራ የነበረው የሰላም ኮንፈረንስ ተጠናቀቀ

By Melaku Gedif

June 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ኮንፈረንስ ተጠናቅቋል፡፡

ትናንትናና ዛሬ በደሴ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሰቆጣ እና ጎንደር ከተሞች የተካሄደው የተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፍረንስ የአቋም መግለጫ በማውጣት ማምሻውን ተጠናቋል።

በአቋም መግለጫቸውም÷ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፈን የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ተወያዮች ባወጡት የአቋም መግለጫ÷ በክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጠይቀዋል።

የመከላከያ ሰራዊት የክልሉን ሰላም ለመመለስ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነትም ምስጋና ቀርቧል፡፡

በክልሉ ህዝብ የሚነሱ የሕገ መንግስት መሻሻልና የወሰን ጥያቄዎች መንግስት ምላሽ እንዲሰጥ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱም ተጠቁሟል።

በክልሉ ያለው የሰላም መደፍረስ በሰላም እንዲፈታ በይቅርታና በሰላም አማራጭ መጓዝ እንደሚገባ ተሳታፊዎች በአቋም መግለጫቸው ጠይቀዋል።

የሀገርን ሰላምና እድገት ለማረጋገጥም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡

በሙሉቀን አበበ እና የክልሉ ኮሙኒኬሽን