Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አርባ ምንጭ ከተማን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርባ ምንጭ ከተማን ጽዱ፣ ውብ፣ ለኑሮ ምቹና ለጎብኚዎች ሳቢ የሚያደርጉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተካሄዱ መሆኑን የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ገለጸ፡፡

የማዘጋጃ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ገዳሙ ሻምበል፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ በተፈጥሮ የታደለቻቸው ሀብቶች ጎልተው እንዲወጡና ተመራጭነቷን ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ልማቱ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው “የጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ ንቅናቄ” በከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በልዩ ትኩረት ለማካሄድ እንዳስቻለ ተናግረዋል።

በዚህም የመንገድ ዳር ቴራዞ ንጣፍ፣ የመናፈሻ ፓርኮች ልማት፣ የመንገድና የውሃ መውረጃ ቦዮች ጽዳት እንደሚያካትት ገልጸዋል።

በተጨማሪም የከተማዋን ገጽታና ውበት የሚጨምሩ የእግረኛ መንገድ፣ የማረፊያ ወንበሮችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ፣ ከተማዋን ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት በይበልጥ ተመራጭ እንደሚያደርጋትም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኮሪደር ልማቱ ከ700 በላይ አባላት ያላቸው 42 ማህበራትን ተጠቃሚ ማድረጉንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

Exit mobile version