አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዝግጅት ሂደት ላይ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ የመንግሥትን ገቢ የመሰብሰብ አቅም የሚያሳድግና ከዚህ ቀደም በተጨማሪ ዕሴት ታክስ ውስጥ ያልተካተቱ አሰራሮችን ለማካተት የሚያስችል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የተጨማሪ እሴት ታክስ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንየህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የተለያዩ ተቋማትና የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ እየተሻሻለ ያለው አዋጅ የመንግሥትን ገቢ የመሰብሰብ አቅም የሚያሳድግና ከዚህ ቀደም በተጨማሪ ዕሴት ታክስ ውስጥ ያልተካተቱ አሰራሮችን ለማካተት የሚያስችል ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላው÷ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጫና እንዳይኖርባቸውና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ የመሆን መብታቸውን በአግባቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አብረሃም አለማየሁ (ዶ/ር)÷ የውሀ እና የመብራት አገልግሎትን በተመለከተ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጫና በማይፈጥር መልኩ አዋጁን ተከትሎ መመሪያ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡
የዱቄት አምራቾች ማኅበር ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን የሚያቀርቡ እንደመሆኑ ተጨማሪ እሴት ታክስ ቀሪ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፣ ሳፋሪኮም፣ የመብራት አገልግሎት፣ ሸማቾች ማኅበር፣ የትራንስፖርት እና የሎጀስቲክ ሚኒስቴር እና የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ረቂቅ አዋጁ ላይ ያላቸውን አስተያየትና ጥያቄ ካቀረቡ ተሳታፊዎች መካከል ናቸው።