ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል በሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

By Melaku Gedif

June 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሊባኖስ የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ይዞታዎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ መወሰኗ ተሰምቷል፡፡

ውሳኔው ሂዝቦላህ የእስራኤል ወታደራዊ ማዕከላትን የሚያሳይ በድሮን የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የተላለፈ እንደሆነ ተነግሯል።

በተጨማሪም ተንቀሳቀሽ ምስሉ የንጹሃን ዜጎችን መኖሪያ፣ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎችን እና የሚሳኤል መከላከያ ባትሪዎችን እንደሚያሳይ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ይህ የሂዝቦላህ ድርጊትም በእስራኤል ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱ ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም እስራኤል በሊባኖስ የሚገኝ ከፍተኛ የሂዝቦላህ አንድ አመራር እና ሶስት ታጣቂዎችን መግደሏ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዳባባሰው ተጠቅሷል።

አሁን ላይም የእስራኤል ጦር ሰሜናዊ እዝ በሊባኖስ የሂዝቦላህ ይዞታዎች ላይ ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የጋዛ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ እስራኤል እና ሂዝቦላህ በሀገራቱ ድንበር አካባቢ ተደጋጋሚ ግጭቶችን ሲያስተናግዱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡