አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2016/17 ምርት ዘመን የመኸር ወቅት እስከ ሰኔ 9 ቀን 2016 ድረስ 13 ነጥብ 63 ሚሊየን ሔክታር በባህላዊና በትራክተር መታረሱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዘንድሮ በመስኖ ስንዴ ልማት 3 ሚሊየን ሔክታር በማረስ 120 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ርብርብ መደረጉን አስታውሶ፤ እስከ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ107 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በዚህም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች 2 ነጥብ 978 ሚሊየን ሔክታር በዘር ተሸፍኗል ብሏል፡፡
የሰብል አሰባሰብ ሥራውም መፋጠኑን ገልጾ፤ እስከ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአጠቃላይ ከ107 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የ2016/17 ምርት ዘመን የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ÷ በሀገሪቱ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታር በማልማት 63 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው ብሏል፡፡
በዚህም እስከ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 3 ነጥብ 559 ሚሊየን ሔክታር ታርሶ 3 ነጥብ 536 ሚሊየን ሔክታር በዘር መሸፈኑን ነው ያረጋገጠው፡፡
በተጨማሪም የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ ሥራ በ2016/17 ምርት ዘመን በሁሉም ክልሎች ከ20 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ሔክታር በማረስ ከ616 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ ውስጥም 12 ነጥብ 125 ሚሊየን ሔክታር በክላስተር የሚለማ መሆኑን እና እስከ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስም 13 ነጥብ 63 ሚሊየን ሔክታር በባህላዊና በትራክተር መታረሱ ተጠቅሷል፡፡
4 ነጥብ 419 ሚሊየን ሔክታሩ ደግሞ በዘር መሸፈኑን ነው ሚኒስቴሩ ያስገነዘበው፡፡