አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁመራ እና አካባቢው በተፈጥሯዊ አደጋ ምክንያት የተቋረጠውን ኃይል መልሶ ለማገናኘት የሚያስችል ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ፡፡
ከሽሬ- ሁመራ በተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ በደረሰ ተፈጥሯዊ አደጋ ኃይል መቋረጡን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ዳይሬክተር ውበት አቤ እንዳስታወቁት÷ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶው የወደቀው ከሁመራ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እንድሪያስ ቀበሌ ነው።
በተፈጠረው የተፈጥሮ አደጋም ሁመራ ከተማን ጨምሮ በዳንሻ፣ ባዕከር፣ አዲረመጥ፣ ሶረቃ፣ ማይካድራ፣ አብደራፊ፣ አብርሃጅራ፣ አዲጎሹ እና አደባይ እንዲሁም በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ከሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ተናግረዋል።
የወደቀውን አንድ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ለመጠገን የቴክኒክ ቡድን በሥፍራው ደርሶ ጥገና መጀመሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ጥገናውን ለማጠናቀቅ እስከ 10 ቀናት ሊፈጅ እንደሚችልም ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ የደረሰው ጉዳት እስኪጠገን ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጥሪ መቅረቡን ከኢትዮጵያ ኤሌክተሪክ ሀይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡