አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያ የሆነው የኢንቨስትመንት ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የክልሉ ም/ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ፀሐይ ወራሳ፣ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ፣ ባለሃብቶች እና የኃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።
የክልሉን ዕድገትና ልማት በማፋጠን የክልሉን ህዝብ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል የኢንቨስትመንት ዘርፍ አንዱ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ፎረሙ በክልሉ ያለውን ጸጋና የመልማት አቅም በመጠቀም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅና ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ለኢንቨስትመንት ምቹና ተስማሚ ከባቢን በመፍጠርና የግል ባለሃብቱን በስፋት በመሳብ የክልሉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በመድረኩ በክልሉ የኢንቨስትመንት አቅምና አመቺነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚደረግ ሲሆን÷ በክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ባለሃብቶች ገለጻ እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡