የሀገር ውስጥ ዜና

የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ የመልሶ ማልማት ስራ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አስችሏል – አቶ ኦርዲን በድሪ

By Feven Bishaw

June 18, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን ህልውና ጠብቆ ለማቆየት የተሰራው የመልሶ ማልማት ስራ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማስቻሉን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

አቶ ኦርዲን በጁገል ዓለም አቅፍ ቅርስ የመልሶ ማልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ዓለም አቀፍ ህያው ቅርስ የሆነውን የጁገል ቅርስ ለነዋሪዎች ብሎም ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ የላቀ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል።

ከጥቂት ወራት በፊት በቅርሱ ዙሪያ ሲስተዋሉ የቆዩ ህገ ወጥ ግንባታዎች እንዲሁም የፅዳት ጉድለት ቅርሱን ለአደጋ አጋልጦት መቆየቱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ቅርሱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመታደግም ማህበረሰቡን ያሳተፈና የተቀናጀ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀው ፥ በተለይም የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማስቻሉን መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቅርሱ መልሶ ልማት ስራ የሐረርን ታሪክ፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ የተከተለና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ያተረፈ መሆኑን በመጠቆም የተጀመረው የመልሶ ልማት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።