የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጥናትና ምርምር ማዕከል ለማቋቋም መከሩ

By Tamrat Bishaw

June 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የአካዳሚክ ጥናትና ምርምር ማዕከላትን ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ምክክር አካሂደዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲን የጎበኘ ሲሆን÷ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጂያ ዌንጂ (ፕ/ር) ጋርም ውጤታማ ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱም የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሰቲ በቻይና የአማርኛ ቋንቋ ኮርሶችን የሚሰጥ ብቸኛው ዩኒቨርሲቲ መሆኑን የገለጹት ሳሙኤል (ዶ/ር)÷ ሌሎች የቻይና ዩኒቨርሲቲዎችም ይህን እንደሚከተሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልዑክ ጉብኝት በቻይና የአማርኛ ቋንቋ ጥናቶች ሂደትን ለመገምገም እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለመቅረጽ ያለመ መሆኑን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡

በኤምባሲው የፖለቲካ እና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኃላፊ አምባሳደር መሀመድ ሰዒድ ሁለቱም ወገኖች ያደረጉትን ጥረት በማድነቅ የምርምር ማዕከላትን በጋራ ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት ኤምባሲው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሰቲ ልዑም በፈረንጆቹ ሐምሌ 1 ቀን 2024 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እንደሚጎበኝ ተመላክቷል።