አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ጠየቁ፡፡
በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ተግዳሮቶችን እና የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በሚመለከት ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
አቶ ኡሞድ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ባለሃብቶች በክልሉ ያለውን እምቅ አቅምና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በብልፅግና ጉዞ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ክልሉ በግብርናው ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎች ያሉትና እምቅ ሀብት ያለው በመሆኑ ባለሃብቶች በፈለጉት የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
መዋዕለ-ነዋያቸውን ፈሰስ ለሚያደርጉ ባለሃብቶች አስፈላጊው መንግስታዊ አገልግሎት በተቀላጠፈ ሁኔታ እንደሚሰጣቸውም አረጋግጠዋል፡፡