የሀገር ውስጥ ዜና

ቻይና ለዩክሬን ቀውስ መፍትሔ ለማምጣት እንደምትሠራ አረጋገጠች

By Meseret Awoke

June 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር በመሆን ለዩክሬን ቀውስ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እንደምታደርግ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን በፈረንጆቹ 2022 ወደ ሩሲያ ከተካተቱት ክልሎች ወታደሮቿን ካስወጣች በኋላ እና ኔቶ የመቀላቀል ዕቅዷን ከተወች ሩሲያ ተኩስ አቁማ ድርድር እንደምትጀምር መናራቸው ይታወሳል።

በፕሬዚዳንቱ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ አስተያየት እንዲሰጥ በተጠየቀው መሰረት “ቻይና ሁልጊዜ በዩክሬን ጉዳይ ላይ ተጨባጭ እና ፍትሐዊ አቋም ትይዛለች” ሲል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

“በቁርጠኝነት እና በንቃት የሰላም ንግግሮች እንዲደረጉ ቻይና ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር ትተባበራለች ፤ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማምጣትም ያላሰለሰ ጥረት ታደርጋለች” ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

ቻይና ከሩሲያ እና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር በትብብርና ዘላቂነት ያለው የደኅንነት ጽንሰ-ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ናት ሲል ሚኒስቴሩ ማረጋገጡን ስፑትኒክ ዘግቧል፡፡