Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) አቅጣጫ መሰረት በጎንደር እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም አበረታች መሆኑ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሠረት በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸም አበረታች መሆኑ ተመላከተ፡፡

በክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር የተቋቋመው ግብረ-ኃይል በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግሥት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ሂደት ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጋር ገምግሟል፡፡

በግምገማውም የአስፋልት መንገድ የሥራ እንቅስቃሴን ጨምሮ የጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል እየተከናወነ ያለውን ሂደትና የመገጭ ግድብ ያለበትን ሁኔታ ተመልክቷል፡፡

የርዕሰ መሥተዳድሩ የመሰረተ-ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ እንደገለፁት÷በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግሥት እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቅንጅት ርብርብ እየተደረገ ነው።

የጎንደር ከተማን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በአጭርና ረዥም ጊዜ በዕቅድ በተያዘው መሰረት በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ ገልጸው÷ የተቆፈሩ የውኃ ጉድጓዶችን በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የመገጭ ግድብ አዲሱ ተቋራጭም በክረምቱ አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅበት ማስገንዘባቸውን የጎንደር ከተማ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል፡፡

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከአዘዞ -ዐርበኞች ዐደባባይ የአስፋልት መንገድ ሥራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የተቋራጩ ውል ተሰርዞ ለኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ከተሰጠ በኋላ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከስትራክቸር ሥራው ጎን ለጎን የአስፋልት ንጣፍ ሥራው ከፍተኛ መሻሻል አለው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የመገጭ ግድብ ለአዲስ ተቋራጭ ውል መሰጠቱን እና በ1 ዓመት ከ6 ወራት ለማጠናቀቅ የጊዜ ገደብ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡

Exit mobile version