አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝት መርሐ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድን፣ በለም አፈር፣ በመልካም የአየር ጠባይ የታደለ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም ለክልሉ ትልቅ የመልማት አቅም ነው ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በግብርና ሥራ ለውጥ ካመጡ ክልሎች አንዱ እንደሆነ በማንሳት÷ ተዘዋውረው የተመለከቷቸው የሌማት ትሩፋት ሥራዎች በአጭር ጊዜ አበረታች ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በኅብረተሰብ ልማት ፕሮጀክት የታቀፈ የሰብል ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት፣ የዶሮ፣ የንብ ማነብ፣ የአሳ እርባታን፣ የሌማት ትሩፋትን ያካተተ ፕሮጀክት እየተተገበረ መሆኑን አይተናል ነው ያሉት።
የኸልዋ አግሮ ኢንዱስትሪ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሥራ መስራቱን ጠቅሰው÷ኢንዱስትሪው የኑሮ ውድነትን በማረጋጋትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ለውጥ ያመጣ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷ ክልሉ ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት በክልሉ በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል።
ክልሉ የዶሮ፣ የሥጋና ሌሎችም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የተያዙ መንደሮችን በመፍጠር ለውጥ አምጪ ሥራ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።