Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሠራዊቱን ኑሮ ለመደጎም እየተሠራ ነው -ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠራዊቱን ኑሮ ለመደጎም እንደተቋም አመርቂ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ጠቅላላ አገልግሎት ዋና ዳይሬክቶሬት የቤቶችና ካምፕ አሥተዳደር ዳይሬክቶሬት የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም÷ በቁርጠኛ የመከላከያ አመራሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማችን የጀመረው የዕድገት ጉዞ በተፈለገው ልክ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም አሁን ላይ የሠራዊቱን ኑሮ ለመደጎም እንደተቋም አመርቂ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ተቋማዊ የሪፎርም ሂደታችን ከዕቅድ አንፃር በሚፈለገው ልክ ግቡን እንዲመታ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የጠቅላላ አገልግሎት ዋና ዳይሬክቶሬት ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ በውስጡ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ በሠራዊቱ ውስጥ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ችግር ፈቺ ተግባራትን መሥራቱን እና ለሌሎቹም አርአያ እየሆነ ያለ ክፍል መሆኑንም በጉብኝታቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በሁሉም የመከላከያ ክፍሎች ውጤታማ የለውጥ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡

Exit mobile version