Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአየር ብክለት ሁኔታ ጠቋሚ ዘመናዊ የራዳር መቆጣጠሪያ ለመትከል እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ብክለት ሁኔታ ጠቋሚ ዘመናዊ የራዳር መቆጣጠሪያ ጣቢያ ለመትከል እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ጣቢያዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚተከሉ የገለጹት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ÷ 250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ መረጃዎችን በፍጥነት መሰብሰብ እንደሚያስችሉ አስታውቀዋል፡፡

የአየር ጠባይና ሁኔታ አመላካች የትንበያ መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን ለቅድመ ማስጠንቀቂያና ልማት ሥራ እገዛ እንዲኖራቸው ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ጠባይ ክስተቶችን ከግምት በማስገባት የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ 1 ሺህ 301 የገፀ-ምድር የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች፣ 300 ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እና ሦስት የከፍታ አየር መመዝገቢያ ጣቢያዎች መተከላቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

Exit mobile version