አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው “ጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄን በሆሳዕና ከተማ አስጀምረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷ አካባቢን ፅዱና አረንጓዴ በማድረግ ድርቅን መከላከልና የከተማ ውበትን መጠበቅ ይገባል።
የዞኑ መንግስት መላውን ህብረተሰብ በማሳተፍ ከተማዋን ፅዱና አረንጓዴ ተወዳዳሪ ከተማ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በበኩላቸው÷ ሆሳዕና ከተማን ፅዱ፣ ማራኪ፣ ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
በዞኑ የከተማ ፅዳትና የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡