Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በድንገተኛ ምርመራ በ1 ሺህ 967 ተሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድንገተኛ ምርመራ ጉድለት በተገኘባቸው 1 ሺህ 967 ተሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ተቋሙ በ67 ተቋማት የተሽከርካሪ የብቃት ማረጋገጥ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የገለጹት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በድሉ ለሌሳ÷ በበጀት ዓመቱ 356 ሺህ ተሽከርካሪዎች በተደረገላቸው ምርመራ ብቁ በመሆናቸው ቦሎ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

ዓመታዊ ምርመራ ከወሰዱ ተሽከርካሪዎች መካከልም 4 ሺህ ያህሉ የብቃት ምርመራውን አለማለፋቸውን ገልጸው÷ ምርመራውን ያላለፉ ተሽከርካሪዎች የወደቁበትን መስፈርት አስተካክለው ድጋሚ ምርመራ በማድረግ ቦሎ መውሰድ እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ ምርመራ በማድረግ ብቃታቸው ተረጋግጦ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም በተለያየ ጊዜ ድንገተኛ ምርመራ እንደሚደረግ ጠቁመው÷ በዚህም በመዲናዋ በተመረጡ ማዕከላት በበጀት ዓመቱ በ5 ሺህ 114 ተሽከርካሪዎች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በፍተሻውም 1 ሺህ 967 ተሽከርካሪዎች ከቀላል እስከ ከባድ ጉደለት እንደተገኘባቸው ገልጸው÷ ተሽከርካሪዎቹ ተገቢውን ቅጣት ተቀጥተውና ጉድለታቸውን አስተካከለው ወደ መስመር መግባታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የክረምት ወቅትም ድንገተኛ ምርመራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማመላከት የተሽከርካሪ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች ብቁ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ብቻ ለአገልግሎት እንዲያውሉ አሳስበዋል፡፡

Exit mobile version