የሀገር ውስጥ ዜና

የማዕድን ኮንትሮባንድ ለመከላከል የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቆመ

By Meseret Awoke

June 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕድን አመራረትን ከማዘመን ባሻገር ኮንትሮባንድን ለመከላከል የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕድን ሚኒስትሩ ሃብታሙ ተገኝ ተናገሩ፡፡

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ 100 ቀናት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተገመገመ ሲሆን ፥ በዚህም የማዕድን ዘርፉን አመራረት የሚያዘምኑ በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ስራ መግባት የሚያስችላቸውን ተግባር እያከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ ሃብታሙ ተገኝ ፥ ኢትዮጵያ በማዕድን ሃብት የታደለች ብትሆንም በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የዘርፉ አሰራር ዘመናዊ መንገድን የተከተለ አለመሆን፣ ሙስና እና ኮንትሮባንድን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ማዕድን ከአምስቱ የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች አንደኛው እንዲሆን መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የማዕድን አመራረትን ለማዘመን እንዲሁም ሌብነትና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ብሔራዊ የማዕድን ካውንስል ተቋቁሞ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ዘርፉ የብዙ ተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ በተለይ ኮንትሮባንድን በመከላከል ረገድ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ማዕድን ዘርፉ አሁን ላይ እየተነቃቃ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ፥ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት አሰራሩን በማዘመን የተሻለ ጥራትና መጠን ያላቸው ማዕድናትን ወደ ውጪ ለመላክ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴን የሚከተሉ በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ምርት ለመግባት የሚያስችላቸውን ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በሚቀጥለው በጀት ዓመት የሲሚንቶ አቅርቦትን አሁን ካለው ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚያሳድጉ ፋብሪካዎች ተጠናቀው ስራ እንደሚጀምሩ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡