አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቆላማ አካባቢዎች ለመስኖ ልማት ያላቸውን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
መንግስት ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማላቀቅ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል ከዝናብ ወቅት ባለፈ የመስኖ ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡
ለአብነትም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተሰጠው ትኩረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል ባለፈ ለወጪ ንግድ ማቅረብ መጀመሯ ይታወቃል፡፡
የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ 100 ቀናት እቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አንዳሉት ፥ ለቆላማ አካባቢዎች ልማት የተሰጠው ትኩረት ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡
ሚኒስትሩ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርና ልማት ትኩረት ከተሰጣቸው ስራዎች መካከል የቆላማ አካባቢዎች የመስኖ ልማት ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያን ከተረጂነት የማላቀቅ ውጥን አካል መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ከዚህ አኳያ በተለያዩ የቆላማ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፥ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም የቆላማ አካባቢዎችን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡