አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ሩሲያ ቭላዲቮስቶክ ከተማ ገብቷል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ሩሲያ ቭላዲቮስቶክ ከተማ የገቡት በብሪክስ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ነው።
ፎረሙ ከሰኔ 9 እስከ 12 ቀን 2016 “ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው፡፡
በፎረም አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ በብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) እና በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ይሳተፋሉ።
ልዑኩ ከፎረሙ ጎን ለጎን የብሪክስ አባል ሀገራት ከሆኑ አቻ የፓርቲ አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያካሔድም ኢዜአ ዘግቧል፡፡