አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የገዛቻቸው አምስት ዘመናዊ የአየር ትራክተሮች በይፋ ስራ ጀመሩ።
የአየር ትራክተሮቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በይፋ ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።
በስራ ማስጀመሪያው መርሐ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የዕጽዋት በሽታ ለመከላከል የኬሚካል ርጭት፣ የአሰሳ ስራ የሚያከናውኑ አምስቱ የአየር ትራክተሮች ለግብርናው ዘርፍ ተጨማሪ መረጃን የሚሰጡና ለተጨማሪ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ተገልጿል፡፡
850 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ የተገዙት የአየር ትራክተሮቹ÷ እስከ 3 ሺህ ሊትር ኬሚካል በአንዴ የመሸከም አቅም ያላቸውና በደቂቃ እስከ 12 ሔክታር መሬት የኬሚካል ርጭት የማከናወን አቅም አላቸው ተብሏል፡፡
የበረሃ አንበጣ፣ ግሪሳ ወፍና ተዛማጅ የሰብል ተባዮችን ለመከላከል፣ የአየር ላይ አሰሳና ቁጥጥር በማድረግ የዕጽዋት በሽታን ለመከላከልም ጥቅም ላይ ይውላሉ ነው የተባለው፡፡
በተለይ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጸረ ሰብል ተባዮችን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው ተብሏል፡፡
የእሳት አደጋን ለመከላከል፣ ዘር ለመዝራት እና ለሌሎች የግብርና ስራዎች አገልግሎት እንደሚውሉም ተጠቁሟል፡፡
የአየር ትራክተሮቹ ለታለመላቸው ዓላማ በማይውሉበት አጋጣሚ በሀገር ውስጥና በውጭ በማከራየት ተጨማሪ ገቢ እንዲያመጡ የሚደረግ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በፍሬህይወት ሰፊው