አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዒድ አል አድሐ በዓልን ሲያከብር በመረዳዳትና በመተዛዘን መሆን እንዳለበትም ርዕሳነ መስተዳድሮች ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ 1 ሺ 445 ኛውን የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷የዓረፋ በዓል ህዝበ ሙስሊሙ ለፈጣሪ በመታዘዝ እርስ በራስ በመደማመጥ በመረዳትና በመተሳሰብ፣ በጎነትን ቸርነትንና ተካፍሎ የመብላትን መንፈሳዊ ክዋኔዎችን በመፈፀም በድምቀት የሚያከብሩት በዓል ነው ብለዋል፡፡
የእስልምና እምነት አስተምህሮ ደግሞ ሰላምን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን እንደሚሰብክ ጠቅሰው÷በዜጎች መካከል አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ይቅር ባይነትን የሚያጎልብትም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አስተምህሮው ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ያሉትን ቅራኔዎች ይፈታል፣ ወደ አንድነትም ያመጣል፣ ሀገራዊ ምክክሩንም የማሳካት ድርሻው ላቅ ያለ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የአረፋ በዓል ሲያከብር የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና ለተቸገሩ ወገኖች የመድረስን ልምድ ለማጠናከር አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስ ልሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡
የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ÷ለመላው የእስልምና አምነት ተከታዮች የኢድ አል-ዓደሃ (አረፋ) በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም÷የኢድ አል-ዓደሃ በዓል አከባበር በሙስሊሙ አምነት ተከታዮች ዘንድ አንዱ የዕምነት ትእዛዝ አካል ሲሆን ድሆችን በመመገብና በመደገፍ የሚከበር በዓል በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች ዘርና ቀለም ሳይለዩ በአመት አንድ ጊዜ በመካ መዲና በሚያደርሱት የሃጂ ሁምራ የአምልኮ ሥርዓት ላይ በአንድ አይነት አለባበስ ስነስርዓት ተክነው ለፈጣሪ ታላቅነትና አምላክነት ስግደት የሚያደርሱበትና አክብሮት የሚሰጡበ እንዲሁም ለሃጢያት ሥርየት ከፈጣሪ ምህረትን የሚለማመኑበት በዓል መሆኑ ታላቅ በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህንን ታላቅ ክብረ በዓል ሲያከብር እንደተለመደው በመረዳዳት፣ በመተዛዘንና ያለው ለሌለው እያካፈለ መሆን እንዳለበትም መግለጻቸውን የየክልሎቹ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡