አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በሀረሪ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የእምነት አባቶችና ተከታዮች 1 ሺህ 445ኛውን የኢድ አል አድሃ በዓል ምክንያት በማድረግ ምዕመናኑ የኢድ ሰላት የሚያደርሱበትን ስፍራ አፅድተዋል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ሀላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ÷ መሰል ተግባራት ክልሉ የሚታወቅባቸውን እሴቶች በማጎልበት ወንድማማችነት እና አብሮነትን በይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።
በዓሉን በወንድማማችነት መንፈስ አንድነትን በሚያጠናክሩ የአብሮነት እሴቶች ማክበር እንደሚገባ እና የአብሮነት እሴቱን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ማህበረሰቡን ያሳተፈ የቅድመ ዝግጅት መደረጉንም መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉ የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች በበኩላቸው÷ምዕመናኑ በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በአብሮነት ማክበር እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።