አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለ ህዝብ ብቁ ተሳትፎ የሚከናወን ስራ ሙሉ ሊሆን አይችልም ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
“ሰላማችንን ዘላቂ እና ህዝባዊ መሰረት ያለው ለማድረግ ዛሬ አሰልጥነን ያስመረቅናቸው 11 ሺህ አዲስ ምልምል የሠላም ሠራዊት አባላትን ጨምሮ 341 ሺሕ የሠላም ሠራዊት አባላትን የከተማችን የሰላም ዘብ አድርገን አሰማርተናል”ሲሉ ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ከ2013ዓ.ም ጀምሮ ነዋሪውን በተደራጀ መልኩ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ማቀናጀት እና የሰላሙ ዋነኛ ባለቤት ማድረግ መቻሉንና እስካሁን ከተገኙት ውጤታማ እና ስኬታማ ስራዎች በተጨማሪ መዲናዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ሰላማዊ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል ፡፡
ሕዝቡ የሰላሙ እና የተሰሩ መሰረተ ልማቶች ባለቤትና ቀዳሚ ተጠቃሚ መሆኑን በመረዳት በየአካባቢያችሁ የሰላምና የመሰረተ ልማቱ ዘብ በመሆን ህዝባችሁን በፍፁም ትህትና እና ፍቅር እንድታገለግሉ ሲሉም ለተመራቂ የሰላም ሰራዊት አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡