የሀገር ውስጥ ዜና

የሪፐብሊካን ጥበቃ ሃይል ለልዩ ተልዕኮ ያሰለጠናቸውን የሰራዊት አባላት አስመረቀ

By Feven Bishaw

June 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሪፐብሊካን ጥበቃ ሃይል ሁሉን አቀፍ ውስብስብ ግዳጆችን በአንድ ጊዜ መወጣት የሚችሉ የልዩ ሃይል አባላትን አስመርቋል።

የምረቃ ስነ ሰርዓቱ ላይ ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና÷ አሁን ላይ የምንገኝበት አለም አቀፍ ሁኔታ ውስብስብና ተለዋዋጭ የጦርነት አውድ የሚያስተናግድ በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህንን የሚመጥን የመከላከያ ሰራዊት እየገነባች ነው ብለዋል።

ሰራዊታችን በፈተና ውስጥም ቢሆን ከእያንዳንዱ ግዳጅ ልምድና ተሞክሮዎችን እየቀሰመና አቅሙን ይበልጥ እያጎለበተ ቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ሰጋቶችን በድል ለመወጣት ሃይሉን ከወዲሁ እያደራጀ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር የሪፐብሊካን ጥበቃ ሃይልም በአራቱም ማዕዘን ችግሮች ሲፈጠሩ ቀድሞ በመድረስ ወሳኝ ሚና የተጫወተ አስተማማኝ ክፍል መሆኑን አንስተዋል።

የዛሬው ስልጠና ሁሉን አቀፍ አቅም ፈጣሪ በመሆኑ ተመራቂዎች ህዝብና መንግስት የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በጥብቅ ዲሲፕሊና ታማኝነት መወጣት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሜጀር ጀነራል አብድሮ ከድር በበኩላቸው÷ የሪፐብሊካን ጥበቃ ሃይል በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር ተሰማርቶ ወሳኝ ድሎችን በማሰመዝገብ ለሰላም መረጋገጥ ትልቅ ዋጋ የከፈለ መሆኑን አውስተዋል።

አሁን የተሰጠው ስልጠናም ትልቅ አቅምን እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ወታደር በየጊዜው የሚሞረድ ሰይፍ መሆን አለበት ብለዋል።

የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይልም ለሚሰጠው ግዳጅ ሁሌም ዝግጁ ሆኖ ከስልጠናው የተገኘውን እወቀት በማዳበር የጠላቶችን ሴራ እየቆራረጠ የሀገር ኩራት መሆኑን ይቀጥላል ብለዋል።

ተመራቂ የሰራዊት አባላትም የተሰጣቸውን ስልጠና ወደ ተግባር በመቀየር ህዝብና መንግስት የሰጣቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።