ዓለምአቀፋዊ ዜና

ህንድ በእሳት አደጋ ህይወታቸውን ያጡ 45 ዜጎቿን አስከሬን ከኩዌት ወሰደች

By Tamrat Bishaw

June 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህንድ አየር ኃይል በኩዌት ህንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ህይወታቸው ያለፈ የ45 ዜጎች አስከሬን ወደ ሀገራቸው አምጥቷል።

የእሳት አደጋው የተከሰተው ከትናንት በስቲያ በኩዌት በማንጋፍ ከተማ 176 ህንዳውያን ሰራተኞች በሚኖሩበት ሕንፃ ላይ ነው።

የኩዌት ባለስልጣናት በአደጋው 50 ሰዎች መሞታቸውን ገልፀው፤ 45ቱ ከህንድ እና 3 ከፊሊፒንስ እንዲሁም የሁለቱ አድራሻ አለመታወቁን ተናግረዋል።

በአደጋው በህንፃው ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ህንዳውያን በመሆናቸው ለህልፈተ ህይወትና ለጉዳት መዳረጋቸው ተመላክቷል።

ከኩዌት ህዝብ ሁለት ሦስተኛው የውጭ ሀገር ዜጎች ሲሆኑ÷ ሀገሪቱ በግንባታ እና በሌሎች የውስጥ ስራዎች በስደተኞች ጉልበት ላይ ጥገኛ መሆኗ ይነገራል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ የሰራተኞቹ የኑሮ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ሲናገሩ መቆየታቸውን የዩፒአይ ዘገባ አመላክቷል።

ከአደጋው በኋላ ወደ ኩዌት ያቀኑት የሕንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ኪርቲ ቫርድሃን ሲንግ ተጎጂዎችን ለመለየት የዘረ መል ምርመራ መደረጉን ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ ዛሬ ማለዳ ላይ በኬረላ ኮቺ ከተማ በማረፍ የሰራተኞቹን አስከሬን ለደቡብ ህንድ ግዛቶች ባለስልጣናት በማስረከብ ወደ ዴልሂ ማቅናቱ ተገልጿል።

የአካባቢው ከፍተኛ ባለስልጣናት በአውሮፕላን ማረፊያው በመገኘት አስከሬኖቹን በክብር የተቀበሉ ሲሆን÷ ለሟች ቤተሰቦችም የግዛቶቹና የፌደራል መንግስት ካሳ እንደሚከፈላቸው ማሳወቃቸውን ዘገባው አያይዞ ጠቅሷል፡፡