ጤና

ስለ ሳንባ ምች ምን ያህል ያውቃሉ?

By Amele Demsew

June 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለይም ለልጆች ሕይወት ማለፍ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ተላላፊ በሽታዎች መካከል የሳንባ ምች በቀዳሚነት እንደሚቀመጥ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡

በሽታው በባክቴሪያ፣ በቫይረስ ወይም በፈንገስ ምክንያት እንደሚከሰት እና የአንዱ ወይም የሁለቱም ሳንባ ኢንፌክሽን ህመም መሆኑን መረጃው ያስረዳል፡፡

የሳንባ ምች በማንኛውም ሰው ላይ የሚከሰት ሲሆን÷ ሕጻናት፣ የዕድሜ ባለጸጋ፣ የልብ፣ የስኳር፣ የሳንባ ህመሞች ያሉባቸው ሰዎች፣ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙ እና አንዳንድ ካንሰሮችን የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ የጤና እክሎች ያሉባቸው ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለሳንባ ምች እንደሚጋለጡም ነው የተጠቀሰው፡፡

ከሳምባ ምች ህመም ምልክቶች መካከልም፦ ትንፋሽ ማጠርና ለመተንፈስ መቸገር፣ ትኩሳት፣ ማቃሰት፣ ትውከት፣ የደረት ውጋት (ህመም)፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ከፍተኛ ድካም፣ መንቀጥቀጥ (ብርድ ብርድ ማለት)፣ ሳል፣ ራስ ምታት ይጠቀሳሉ ፡፡

ጉንፋን የተለመደ የሳንባ ምች መንስኤ በመሆኑ ራስን ከጉንፋንና መሰል በሽታዎች መከላከል እንደሚገባ ይመከራል፡፡

የሳንባ ምች ህመም ያለበት ሰው÷ በሐኪም የታዘዘለትን መድኃኒት ሳያቋርጥ መውሰድ፣ በአግባቡ ምግብ መመገብ፣ በቂ ፈሳሽ መውሰድ፣ እረፍት ማድረግ፣ ራስ ምታቱን መቆጣጠር እንዲሁም የኦክስጅን ሕክምና መውሰድ በሽታው እንዳይባባስና ሌሎች ተጓዳኝ የጤና እክሎች እንዳይከሰቱ ያግዛል ብሏል መረጃው፡፡