የሀገር ውስጥ ዜና

የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ ነው ተባለ

By Feven Bishaw

June 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱን የሃብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለው ሥራ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናገሩ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትሯ÷ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያደርገውን አስተዋጽዖ ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውጭ ሀገር የቱሪዝም ፍሰቶችን የማስተዋወቅና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር እንዲሁም መዳረሻዎችን የማስፋትና ነባሮችን የማደስ ሥራ ለውጤቱ መገኘት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተናግረዋል።

የኮንፈረስ ቱሪዝም በማስፋፋት ረገድ ባለፉት 10 ወራት በጤና፣ በትምህርት፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎችም ዘርፎች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ በማመቻቸት ገቢን የማሳደግ ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል።

በርካታ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውና የገበታ ለትውልድ ሥራዎችን በመጀመር ዘርፉን እድገት ለማፋጠን ተሰርቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሚኒስትሯ በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ነባር የቱሪስት መዳረሻዎች ገበያው በሚፈልገው ልክ እንዲሆኑ ያደርጋል ነው ያሉት።

ባለፉት 100 ቀናት በሀገሪቱ ተወዳዳሪ ሆቴሎች እንዲኖር ደጃዎችን የመመደብ ሥራ መሰራቱንም አክለው ጠቅሰዋል።

ባለፉት 10 ወራት የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥርና ገቢን ለማሳደግ እየተሰራው ያለው ሥራ ሚኒስቴሩ ከያዘው እቅድ አንጻር ውጤታማ እንደነበር አስገንዝበዋል።

ሀገሪቱ ካለት እምቅ አቅምና ፍላጎት አንጻር ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረው፤ በቀጣይ ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የመጓጓዣ አገልግሎት በማቅረብ ቱሪዝም ዘርፉ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።