የሀገር ውስጥ ዜና

ም/ጠ/ሚ ተመስገን የተገኙ የልማት ስኬቶችና ዕድገቶች ላይ መቆም እንደማይገባ አስገነዘቡ

By Tamrat Bishaw

June 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተገኙ የልማት ስኬቶችና ዕድገቶች ላይ መቆም የለብንም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገነዘቡ።

የ2016 ዓ.ም የ10 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች ዋና ዋና አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል።

በመርሀ-ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ሚኒስትሮችና የተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ÷ የሀገርን ዕድገት እውን ለማድረግ ያልተቆራረጠ ስራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የሀገርን ጸጋ የተረዳ ዕይታ፣ ድልን የመጠበቅ ሳይሆን የተገኘን ድልና ስኬት ለማስቀጠል መትጋት፣ በየትኛውም ዘርፍ የተገኘን ስኬት የጋራ ድል አድርጎ ለተሻለ ስኬት መስራት ይገባልም ነው ያሉት።

የመንግስት ቀጣይ አራት ምሰሶዎች የተባሉ ጉዳዮችን ያብራሩት አቶ ተመስገን÷ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፣ የሪፎርም ስራዎችን ማስቀጠል በተለይ ደግሞ በሲቪል ሰርቪስ የሪፎርም ስራ በማስቀጠል ፈጣን፣ ፍትሃዊና አካታች አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ በአጽንዖት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ሀገራዊ ምክክሩን ጨምሮ የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፤ የትውልድ ምርታማነት በተለይም ትምህርት ጤናና ሌሎች የማህበራዊ ልማትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

መንግስት ስራዎችን ለየት ባለ መንገድ ለመተግበር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ይህን ወቅት እንደቀደመው በዝግጅት አናሳልፍም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም እስከ ሰኔ 30 ድረስ ስራን ከማከናወን ተግባር ጎን ለጎን የተሰሩ ስራዎችን መገምገም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከበጀት አመቱ 10 ወራት አፈጻጸም በተጨማሪ የ2017 የትኩረት አቅጣጫዎችን የተመለከተ ውይይት ይደረጋል።

በፍሬህይወት ሰፊው