የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅዱን አስተዋወቀ

By Tamrat Bishaw

June 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅዱን ይፋ አድርጓል፡፡

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ እንዳሉት÷ እቅዱ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፣ ከአውሮፓ የምርጫ ድጋፍ ማዕከልና የምርጫ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን በተገኘ ድጋፍ እና በባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት የተዘጋጀ ነው።

ስትራቴጂያዊ እቅዱ ቦርዱ የምርጫ ሒደቶችን በራሱ አቅም የሚያከናውንበትን ችሎታ ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

መጪውን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ እና የአካባቢ ምርጫዎች ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት መሰረት እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

ቦርዱ ይህንን የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ስልታዊ ግቦች እና አላማዎች ለማስፈጸም ቁርጠኛ መሆኑን ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል።

ስትራቴጂያዊ እቅዱ ሁሉም የቦርድ አመራር አባላት፣ የስትራቴጂ እቅድ ዝግጅት ኮሚቴ እና የአጋር አካላት የጋራ አመራር እና ድጋፍ ውጤት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በይስማው አደራው