የሀገር ውስጥ ዜና

ዩኒቨርሲቲዎች ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ትምህርት እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

By Melaku Gedif

June 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ትምህርት እንዲጀምሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩም የትምህርት ሚኒስቴር አፈፃፀም በስፋት ውይይት የተደረገበት መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ከማኅበረሰቡ በተገኘ ድጋፍ በትምህርት ለትውልድ መርሐ ግብር 22 ሺህ የሚደርሱ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታና ጥገና መከናወኑን አስታውቀዋል።

በተለይም ለተማሪዎች የሚሰጠው የሪሚዲያል ፈተና መጀመሩን በማስታወቅ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና መሰጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መሰጠት እንደሚጀምር የገለጹት ሚኒስትሩ÷ ፈተናውን የተሳለጠ ለማድረግ ለፈታኝ መምህራን በቂ ሥልጠና እየሰተጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በወረቀትና በኦንላይን የሚሰጥ መሆኑን ተከትሎ ለዚህ የሚረዳ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በክረምት ወራት 62 ሺህ መምህራንን በሚያስተምሩት ትምህርትና የማስተማር ሥነ ዘዴ ዙሪያ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩ በክረምት ከያዛቸው ሥራዎች መካከል የዩኒቨርሲቲዎች ዕድሳት ሥራ አንዱ በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመጪው ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ትምህርት እንዲጀምሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የመጽሓፍት ሥርጭትን በተመለከተ አሁን ላይ ጥምርታውን አንድ መጽሃፍ ለሶስት ተማሪ ማድረስ መቻሉን አንስተዋል።

በቀጣይ ሁለት ወራት ሚኒስቴሩ ያዘዛቸው መጽሃፍት ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ በመሆኑ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከሞላ ጎደል ለእያንዳንዱ ተማሪ አንድ አንድ መጽሃፍ ማዳረስ እንችላለን ሲሉ ገልጸዋል።

ከዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።