Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 24 ሀገራት የሚሳተፉበት የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት 4 ሠዓት ላይ አስተናጋጇ ጀርመን ከስኮትላንድ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል፡፡

ጨዋታው ሲቀጥል ነገ ቀን 10 ሠዓት ላይ ሀንጋሪ ከስዊዘርላንድ፣ ምሽት 1 ሠዓት ላይ ስፔን ከክሮሽያ እንዲሁም ምሽት 4 ሠዓት ላይ ጣልያን ከአልባኒያ ይጫወታሉ፡፡

በምድብ ማጣሪያው በምድብ አንድ ጀርመን፣ ስኮትላንድ፣ ሀንጋሪ እና ስዊዘርላንድ ሲደለደሉ÷ በምድብ ሁለት ደግሞ ስፔን፣ ክሮሽያ፣ ጣልያን እና አልባኒያ ተመድበዋል፡፡

በምድብ ሦስት የተደለደሉት ደግሞ ስሎቬኒያ፣ ዴንማርክ፣ ሰርቢያ እና እንግሊዝ ሲሆኑ÷ ፖላንድ፣ ኔዘርላንድስ (ሆላንድ)፣ ኦስትሪያ እና ፈረንሳይ ደግሞ በምድብ አራት ተደልድለዋል፡፡

ቤልጂየም፣ ስሎቫኪያ፣ ሮማንያ እና ዩክሬን በምድብ አምስት እንዲሁም ቱርክ፣ ጆርጂያ፣ ፖርቹጋል እና ቼክ ሪፐብሊክ በመጨረሻው ምድብ መደልደላቸውን የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ያወጣው መርሐ-ግብር ያመላክታል፡፡

በወጣው መርሐ-ግብር መሠረትም ጨዋታው እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ውድድሩ በ10 ከተሞች የሚካሔድ ሲሆን የመክፈቻው ጨዋታ በሙኒክ ከተማ አሊያንዝ አሬና እንዲሁም የፍፃሜው ጨዋታ በበርሊኑ ኦሎምፒክ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ከ650 ሺህ የሚበልጡ የተለያዩ ሀገራት ደጋፊዎች ወደጀርመን ያቀናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡

እስከ አሁን ባለው የውድድሩ ታሪክ ጀርመን እና ስፔን እኩል ሦስት ዋንጫዎችን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆኑ÷ ፈረንሳይ እና ጣልያን ደግሞ እኩል ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ከፍ አድርገዋል።

የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት፣ ፖርቹጋል፣ የቀድሞዋ ቼኮስሎቫኪያ፣ ሆላንድ፣ ዴንማርክ እና ግሪክ ደግሞ አንድ ጊዜ ዋንጫውን መውሠድ ችለዋል።

በሌላ በኩል ዩሮ 2024 ለፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ስድስተኛ ተሳትፎው ሲሆን÷ የመድረኩ የመጨረሻ ተሳትፎው እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሮናልዶ እስካሁን በአውሮፓ ዋንጫ ተሳትፎው 14 ጎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ክብረወሠን ባለቤት መሆኑም ይታወቃል።

Exit mobile version