አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቶችን ማብቃት፣ ድምጻቸውን ማሰማት፣ ሃሳባቸውን መለዋወጥ እና ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት የሚያስችል “ዩ ሪፖርት ኢትዮጵያ” የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ተደርጓል፡፡
መተግበሪያውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር ነው ይፋ ያደረጉት፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ፥ መተግበሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች በተለይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲለዋወጡ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል።
ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ከወጣቶቹ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋልም ነው ያሉት።
የወጣቶችን ድምጽና ሃሳብ የምንሰማበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ ወጣቶች መተግበሪያውን በመጠቀም ለዘላቂ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።
በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በጥልቀት እየመከረች የምትገኝ ወቅት በመሆኑ ወጣቱ በንቃተ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ወጣቶች መተግበሪያውን ፍሬያማ በሆነ መንገድ፣ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት እንዲገለገሉም በአጽዕኖት ማሳሰባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው ÷ “ዩ ሪፖርት ኢትዮጵያ” ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል መተግበሪያ መሆኑን ጠቁመው÷ በ99 የዓለም ሀገራት ተግባራዊ ሲደረግ እንደነበር ገልጸዋል።