አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጎል በልብስ መሳይ ሽፋን የተሸፈነ ነው፤ ሽፋኑ (Meninges) አንጎልን ሸፍኖ ከልዩ ልዩ ባዕድ ነገሮች ይጠብቃል፤ ወጪና ገቢ ምልልሶች በምጥጥን እንዲከወኑና ጤናማ ዑደት እንዲኖራቸው ያግዛል።
የአንጎል ሽፋን ብግነት ደግሞ ማጅራት ገትር ህመም ይባላል፡፡
ህመሙ በልዩ ልዩ ህመም አምጪ ተህዋሲያንና ባዕድ ነገሮች የሚፈጠር አደገኛና አጣዳፊ ሲሆን÷ በተለይ በባክቴሪያ የሚመጣው ማጅራት ገትር በቶሎ ካልታከመ ህይወትን ሊነጥቅ የሚችል ከባድ ህመም ነው።
በማጅራት ገትር በተለየ ሁኔታ ተጠቂ የሚሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች ህፃናት፣ አዛውንቶች፣ የካንሰር ታማሚዎች፣ የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚዎች፣ የአካል ንቅለ ተከላ ያካሔዱ፣ ኬሞቴራፒ የወሰዱ፣ ለብዙ ጊዜ እስቴሮይድ የሚወስዱ፣ የምግብ እጥረት፣ በተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል ድክመት ያለባቸውና ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች ናቸው።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ማንም ሰው ከማጅራት ገትር ተጋላጭነት ነፃ አይደለም።
ማጅራት ገትርን መከላከል ይቻላል፤ ከመከላከል አልፎ በበቂ እና አስተማማኝ ህክምና መፈወስ የሚቻል ሲሆን÷ በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል በሚሰጥ ክትባት አማካኝነት ይህንን ገዳይ ህመም የሚያመጡ ዋና ጀርሞችን ማክሸፍ ተችሏል።
በዚህም ልጆችን በማስከተብ ገዳይ የሆነውን ማጅራት ገትር መከላከል እንደሚቻል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም ጉንፋን፣ የጆሮ ኢንፌክሽን፣ የቶንሲል ኢንፌክሽን፣ የሳንባ ኢንፌክሽን፣ እንዲሁም የጭንቅላት ቅል ምት ህመሞች ካጋጠሙ ይህንን በማስታከክ ማጅራት ገትር ሊከሰት ስለሚችል ህመሞቹን በቶሎ ማከም አሊያም እንዳይፈጠሩ ማድረግ ይገባል።
ማጅራት ገትር በህፃናት ላይ ሲከሰት በአዳጊ አንጎላቸው ላይ መስተጓጎልን በመፍጠር ልጆችን ለልዩ ልዩ የአንጎል ህመሞች ይዳርጋል።
በዚህም ለስትሮክ፣ ለአንጎል ንዝረት፣ ለመስማት ችግር፣ ለንቃተ ህሊና መድከም፣ የአስተሳሰብ እና ትምህርት አቀባበል ችግሮች፣ ለአይነ ስውርነት ይዳርጋል፡፡
ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማንቀጥቀጥ፣ የንቃት መውረድ፣ አንገትን ማጠፍ አለመቻል/መገተር፣ እራስ ምታት ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ካሉ የማጅራት ገትር ህመም ምልክቶች በመሆናቸው በፍጥነት ሐኪም ማማከር ይገባል።