አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት ያለፉት 10 ወራት ከ3 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።
ሚኒስትሯ ፥ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተፈላጊውን ክህሎት እንዲጨብጡ የማብቃት ተግባር ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
በተለይም የሠለጠነ የሰው ኃይል ወደ ውጭ ለማሰማራት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፥ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ ብቁ ስለመሆናቸው የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
314 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሥራ ስምሪቱ ዜጎች ደህንነታቸው፣ የሚያገኙት ጥቅምና መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ በሚያስችል መልኩ መከናወኑንም ነው ያብራሩት።
በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በጥቅሉ ለ3 ሚሊየን 77 ሺህ ዜጎች የሀገር ውስጥና የውጭ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
የዲጂታል ሥርዓት በመዘርጋት ዜጎች ተመዝግበው ወደ ሥራ ገበያው እንዲገቡ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይም በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በቴክኒክና ሙያ ዘርፍም ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ ሃሳብ ወደ ቴክኖሎጂ ምርት መቀየር የሚችሉበት ስልጠና እና ምቹ ምህዳር መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም የስራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በማወዳደር ምርቶቻቸውን ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲጠቀሙ በተጀመረው ሂደት 76 ቴክኖሎጂዎች ወደ ምርት መሸጋገራቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ስታርት አፖችና ኢንተርፕራይዞችን በማጎልበት ተጨማሪ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ በመንግስት ትኩረት መደረጉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።