Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የበጀት ዓመቱ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የዘር ሽፋን ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጀት ዓመቱ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የዘር ሽፋን ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩም የግብርና ስራዎች አፈፃፀም በስፋት ውይይት የተደረገበት መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የ2015/16 የምርት ዘመን ከታቀደው እቅድ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ምርት የተሰበሰበበት መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የላቀ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው÷በዚህም 3 ሚሊየን ሄክታር በዘር ተሸፍኖ 106 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በበልግም 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በመዝራት ከእቅዱ በላይ ተሳክቷል ነው ያሉት።

ለግብርና ልማት የግብዓት አቅርቦት ዘንድሮ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው÷ በተለይም በአፈር ማዳበሪያ ግዥና ስርጭት የተሻለ አፈፃፀም መኖሩን አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት በ930 ሚሊየን ዶላር የተገዛው 20 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከአምናው የ6 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረገና በዜጎች አኗኗር ላይ እመርታዊ ለውጥ ያመጣ መሆኑንም አንስተዋል።

Exit mobile version