Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኮንጎ በደረሰ የጀልባ አደጋ ከ80 በላይ መንገደኞች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ አቅራቢያ በሚገኝ ወንዝ ላይ 270 በላይ ተሳፋሪዎችን ጭና የነበረች ጀልባ ተገልብጣ ከ80 በላይ መንገደኞች ህይወት ማለፉን ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ትሺሴኬዲ አስታውቀዋል።
 
በሀገሪቱ በፈረንጆቹ የካቲት ወር ላይ ከአቅም በላይ የጫነች ጀልባ በመስጠሟ የበርካቶች ህይወት መቀጠፉ ይታወሳል፡፡
 
የአሁኑ ክስተትም በጀልባዎች ከአቅም በላይ መጫን ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ትችት በሚሰነዘርባት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የደረሰ የቅርብ አሳዛኝ አደጋ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
ፕሬዚዳንቱን ዋቢ አድርጎ የወጣ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በአካባቢው የተሰራች ጀልባ በማይ-ንዶምቤ ግዛት ክዋ ወንዝ ላይ ተገልብጣለች።
 
በሞተር ብልሽት ምክንያት የተሰናከለችው ጀልባ 271 ሰዎችን አሳፍራ ወደ ኪንሻሳ ስትጓዝ እንደነበርና ከወንዙ ዳርቻ ጋር ተጋጭታ መሰበሯን የአካባቢው ሬዲዮ ጣቢያ የሙሺ ወረዳ የውሃ ኮሚሽነር ሬን ማከርን ጠቅሶ ዘግቧል።
 
ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ የ86ቱ ህይወት ሲያልፍ፣ ቀሪዎቹ ወደ ባህር ዳርቻ በመዋኘት መሻገር መቻላቸውን ሜከር ተናግረዋል።
 
የኮንጐ ባለስልጣናት ከመጠን በላይ መጫንን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ሲያስጠነቅቁ መቆየታቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ የውሃ ላይ መጓጓዣ የደህንነት ሥርዓቶችን በሚጥሱ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ መናገራቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
Exit mobile version