አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “የግብር አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በማዘመን ያሉትን ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም የገቢ አሰባሰብ አፈፃፀምን ማሳደግ ይገባል” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥላሁን ከበደ አሳሰቡ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ2016 በጀት ዓመት የሀብት አስተዳደርና የገቢ አሰባሰብ ስራዎች ልዩ የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ÷ የገቢ አሰባሰብ አቅም ያለበትን ደረጃ እንዲሁም እስከ አሁን የተሰበሰበውን ገቢ እና የወጣውን ወጪ በመገምገም በቀሪ ጊዜያት በቁጭት ወደ ተግባር መግባት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ግብርን በተገቢው መንገድ የማይሰበስብ መንግስት ለህብረተሰቡ የመልማት ጥያቄ ምላሽ መስጠት አይችልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በማዘመን ያሉትን ፀጋዎች በመለየት ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አብራርተዋል።
ክልሉ በርካታ ፀጋዎች ቢኖሩትም ባለፉት 10 ወራት ክልሉን የሚመጥን ገቢ አልተሰበሰበም ያሉት አቶ ጥላሁን÷ ከግብር አሰባሰብና አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን በእውቀት በማረም ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።