Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት እየተረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት እየተረገ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ÷ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሚያቀርቡት መሰረተ ልማት የአገልግሎት ወጪን ሸፍኖ ተመጣጣኝ ትርፍ የማግኘትና በመንግሥት በኩል ደግሞ ለህዝቡ ኤሌክትሪክ ተደራሽ የማድረግ አላማን ፍትሃዊ በሆነ አግባብ እንዲፈጸም የማድረግ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

ይሁንና በተቀመጠው የህግ አግባብ የሁሉንም አካላት ፍላጎት አስጠብቆ ለማስቀጠል አዳጋች የሆኑ የዘርፉ ዕድገት ማነቆዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ መንግስት ህብረተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ላለማድረግ ሲል በህግ የተቀመጠውን የታሪፍ ማሻሻያ ጊዜ ጠብቆ እንዲከለስ አለማድረጉን ጠቁመዋል።

ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም በየዓመቱ ተግባራዊ የተደረገው የኤሌክትሪክ ታሪፍ በ2014 ዓ.ም የተጠናቀቀ ሲሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለምንም ማሻሻያ መቆየቱን አንስተዋል።

ይህ ሁኔታ ተቋማቱ ጥራት ያለውና አስተማማኝ አገልግሎት እንዳያቀርቡ ፣ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የፋይናንስ ዕጥረት እንዲገጥማቸውና ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ እንዲዘፈቁ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በተጨማሪም የሀይል አቅርቦት አማራጮችን ለማስፋት እና በኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ዘርፉን ለመደገፍ አሁን ባለው ታሪፍ ማሰብ ፈታኝ እንደሆነም አንስተዋል።

በዚህም የሀይል አቅራቢ ተቋማቱ የታሪፍ ጥናት አዘጋጅተው ለባለስልጣን መስሪያቤቱ ባቀረቡት መሰረት ታሪፍ ቅድመ ግምገማ በማከናወን ከህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች አስተያየት እንቀበላለን ነው ያሉት ወ/ሮ ሳህረላ።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version